በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለሌሎች አፍሪካ ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለሌሎች አፍሪካ ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለሌሎች አፍሪካ ከተሞች በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑ ተገለጸ።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከንቲባዎችና ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ የተሰሩ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የዛንቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ ከንቲባ ቺላንዶ ቺታንጋላ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለልጆች ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት የፕሮግራም ትግበራ ለሉሳካ እና ሌሎችም የአፍሪካ አገራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
የሴራሊዮን ጤና ሚኒስትር ኦስቲን ዴምባይ (ዶ/ር)፤ በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን አድንቀዋል።
የልማት ፕሮግራሙ ለሌሎች አፍሪካ ከተሞች በምሳሌነት የሚጠቀስ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ ሕፃናት የተሟላ የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ስለመኖራቸውም ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ ዙር 2 ሺህ 200 ባለሞያዎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ ወደ ስራ ማሰማራቱን አስታውሰው በዛሬው እለትም ተጨማሪ 3 ሺህ 85 ማሰልጠኑን ተናግረዋል።
ከጉብኝቱ በኃላ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በመሪነት ዘመናቸው የነበረን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ትግበራ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተከዜ ተፋሰስ አካባቢ የመቀንጨር ችግርን በሙሉ ማጥፋት ግብ የሰነቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ነፍሰ-ጡር እና ወላድ እናቶች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የሥርዓተ-ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩም በየአመቱ 3 በመቶ የመቀንጨር ችግርን በመፍታት እ.አ በ2022 ብቻ 100 ሺህ ህፃናት ከመቀንጨር ችግር እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።
የሰው ልጆችን የክህሎት፣ የምርምርና ፈጠራ አቅም ለማሳደግ ከህፃንነት ጀምሮ ተገቢ የሆነ ክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው የአፍሪካ አገራትም በዚህ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።