ቀጥታ፡

የህዝባችንን ትስስር የሚያጠናክር የአንድነት ድልድይ  የመገንባት ተግባር እየተከናወነ ነው -  ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

ባህር ዳር ፤ ግንቦት 4/2016 (ኢዜአ)፡- በመሰረተ ልማትና በአስተሳሰብ ግንባታ ላይ በማተኮር የህዝባችንን ትስስር የሚያጠናክር የአንድነት ድልድይ የመገንባት ተግባር በማከናወን ላይ እንገኛለን ሲሉ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር በመሆን ነው አዲሱን የዓባይ ድልድይ የመረቁት።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እና ሚኒስትሮች ተገኝተዋል። 

ከአራት ዓመት ተኩል በፊት ግንባታው ተጀምሮ የተጠናቀቀው አዲሱ የዓባይ ዘመናዊ ድልድይ የ380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር ስፋት አለው።  

በሁለቱም የመንገድ ክፍል ባለሶስት መስመር የተሽከርካሪ መንገድ ያለው ሲሆን፤ በጎን የብስክሌት መጋለቢያ መስመር ተዘጋጅቶለታል።

በዓባይ ድልድይ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤  የልዩነት ግድግዳን በማፍረስ የጋራ ትርክት መገንባት የሚቻለው ሀገራችን በመሰረተ ልማትና በሌሎች ፕሮጀክቶች በማስተሳሰር መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

በሀገር ደረጃ የሚገነቡ የመሰረተ ልማት፣ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች የግንባታ ስራዎች "የምንመኛትን የበለፀገች ኢትዮጵያ ለማየት መሰረት ናቸው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የዓባይ ድልድይ ለህዝቦች ትስስር፣ ለንግድ ልውውጥና ለቱሪዝም ስራዎች መፋጠን ታላቅ አበርክቶ አለው።

አዲሱ የዓባይ ድልድይ ህዝቦችን በማስተሳሰር የአንድነት ትርክትን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። 

የክልሉ ህዝብ የተፈጠረውን እድል በመጠቀም አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ከተጠቃሚነት በማለፍ ለትውልድ መስራት አለበት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)። 

መንግስትም አዲሱን የዓባይ ድልድይ ግንባታ በማስመረቅ፣ የገበታ ለሃገርና የገበታ ለትውልድ አካል የሆኑት የጎርጎራና የሎጎ ሃይቅ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን አንድ በማያደርግ፣ ለሰላም በማይጠቅምና ለህዝቦች እኩልነት በማያመጣ የጥፋት ጉዞ የሚሳተፉ ከዚያ ወጥተው ለክልሉ ሰላምና ልማት ከክልሉ መስተዳድር ጋር በትብብር ሊሰሩ ይገባል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው አዲሱ ድልድይ ክልሉንና የባህር ዳር ከተማን የልማት የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ድልድዩ ለንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ሌሎች የልማት ስራዎችን ለማስፋፋት ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር፤ ለከተማዋ ልክ እንደ ዘንባባዎቿና የጣና ሃይቅ ዋና ምልክት ሆኖ የሚያገለግል አሻራ እንደሆነም ተናግረዋል።

የድልድዩ መገንባትም በቀጣይ የዓባይ ወንዝ ዳርቻን መሰረተ ያደረገ ልማት በማከናወን ተመራጭ ከተማ ለመፍጠር በትኩረት ለመስራት እድል የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። 

  

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሃመድ አብዱራህማን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የእግረኛና የብስክሌት መተላለፊያ መንገድን አካቶ ዘመኑ የደረሰበትን የግንባታ ቴክኖሎጂን ተጠቅሟል።

የዓባይ ድልድይ ለአንድ መቶ ዓመት የማገልገል አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።

እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የድልድዩን ክብደት ለመቀነስም በ72 ኬብሎች ተወጥሮ የተገነባ ነው።  የአራት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር መዳረሻ የአስፋልት መንገድና የመብራት ጨምሮ ሌሎችም ግንባታዎች አሉት።

 
 

 የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ የአዲሱ የዓባይ ድልድይ መጠናቀቅ ፈተናዎችን በመሻገር ከፍታ ላይ ለመድረስ የያዝነው የብልጽግና ጉዞ እንደሚሳካ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም