ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ  ለጽዱ ኢትዮጵያ ዲጂታል ቴሌቶን ንቅናቄ የድጋፍ  መረሃ ግብር ተካሄደ

ባህር ዳር ፤ ግንቦት 4/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ ዲጂታል ቴሌቶን ንቅናቄ የድጋፍ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚነስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የድጋፍ መርሃ ግብሩን አካሂደዋል። 


 

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን ያደረጉት  ዛሬ በተከናወነው  የዓባይ ድልድይ የምረቃ ስነ-ስርዓት ለመታደም ባህር ዳር በተገኙበት  ወቅት ነው።

በዚህ ወቅት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  አነሳሽነት የተጀመረው “የጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ንቅናቄ እውን እንዲሆን ህብረተሰቡ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የዛሬው ለጽዱ ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴሌቶን ንቅናቄ መርሃ-ግብር የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዲጂታል ቴሌቶን መርሃ-ግብሩም 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና በየደረጃው ያሉ የአመራር አባላት ''ለጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና'' ንቅናቄ  እውን መሆን ገንዘብ ሲያዋጡ መቆየታቸውን አውስተዋል።

በአንድ  ጀንበር  50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደው የዲጂታል ቴሌቶን ንቅናቄ  ከእቅዱ እንደሚልቅ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ተመስገን ገለፃ፤  እየደረሰ ባለው መረጃ መሰረትም በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ደጋፊዎች በንቅናቄው በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ  ከኒዮርክና ጀኔቫ በመቀጠል ብዙ ዲፕሎማቶች የሚኖሩባት ከተማ እንደመሆኗ መጠን  ጽዱና ለኑሮ ተስማሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ''የጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና'' ዓላማም ይሄ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ጽዱና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ ማስቻል ዋና ዓላማ ያደረገ ንቅናቄ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

ጽዱ ከሆነ አካባቢ ጽዱ የሆነ አስተሳሰብ እንደሚፈልቅ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን እውን ሊያደርግ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

''የፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና'' መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን  ግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘብ በማዋጣት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም