የኢትዮጵያ አትሌቶች በሩጫ ከማሸነፍም ባለፈ ለውበትና ጽዳት አርአያ በመሆን የሀገራችሁን ውበት መግለጥ አለባችሁ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አትሌቶች በሩጫ ከማሸነፍም ባለፈ ለውበትና ጽዳት አርአያ በመሆን የሀገራችሁን ውበት መግለጥ አለባችሁ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቶች በሩጫ ከማሸነፍም ባለፈ ለውበትና ጽዳት አርአያ በመሆን የሀገራችሁን ውበት መግለጥ አለባችሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ለፅዱ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የማሰባሰብ የዲጂታል ቴሌቶን ከማለዳው ሁለት ሰአት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች የ“ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” ንቅናቄን ተቀላቅለዋል።
በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ እየተከናወነ ያለውን ዲጂታል ቴሌቶን በመቀላቀልም ድጋፋቸውን አሳይተዋል።
በዚሁ ሁነት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የ“ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” ንቅናቄ አላማ ገንዘብ ማዋጣት ብቻ ሳይሆን ሀገርን ንፁህ የማድረግ አላማ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቶች በአሸናፊነት የሀገራችሁን ሰንደቅ አላማ ከፍ እንዳደረጋችሁ ሁሉ ጽዱ ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ግንባር ቀደም ልትሆኑ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለኑሮ ምቹና በተፈጥሮ ሃብትም የታደለች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው አትሌቶች በሩጫ ከማሸነፍም ባለፈ ለጽዳት አርአያ በመሆን የኢትዮጵያን ውበት መግለጥ አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በተባበረ መንገድ ያማረችና ንፁህ ሀገረ መገንባት አለብን ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።