በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለው የስፖርት አቅም ጎልቶ እንዲወጣ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለው የስፖርት አቅም ጎልቶ እንዲወጣ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ
ቦንጋ፤ ግንቦት 4 / 2016 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለው የስፖርት አቅም ጎልቶ እንዲወጣ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በተገኙበት የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የችቦ መለኮስ፣ የውድድርና ሌሎችም መረሃ ግብሮች በቦንጋ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
በዚህ ወቅት እንደተመለከተው፤ ክልሉ በሩጫው የአገሪቱን ስም በአለም መድረክ ከፍ አድርገው በማስጠራት ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል እነ ታደሰ ወርቁና ሂሩት መሸሻ እንዲሁም በብስክሌት ወጣት በረከት ወንድሙ ይጠቀሳሉ።
ሆኖም ክልሉ በዘርፉ ያለውን አቅም አውጥቶ መጠቀም በሚያስችል መልኩ ተገቢውን ትኩረት እንዳላገኘና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ደጋፊዎች ጠይቀዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የካፋ ቡና አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ፍቃዱ ገዛሃኝ እንዳሉት፤ ከአስር ዓመታት በፊት ስራ የጀመረው ክለቡ በትኩረት ማጣት ችግር አጋጥሞት ቆይቷል።
ይህም ሆኖ ክለቡን ለማጠናከር በተደረገው ጥረት በ2016 ዓ.ም ታህሳስ ወር በራሱ ተነሳሽነት 54 ወጣቶችን መልምለው በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ክልሉ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ስፖርተኞች ቢኖሩትም ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቅሰው፤ ክልሉ በዘርፉ ያለውን አቅም አጉልቶ እንዲያወጣ በሚመለከተው አካል ድጋፍና እገዛ እንዲደረግለት ጠይቀዋል።
በራሳቸው ተነሳሽነት በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ሂኒጊዶ ቀበሌ ተሰጥኦ ያላቸውን 38 ወጣቶችና ታዳጊዎችን በመመልመል የስፖርት ባለሙያ ቀጥረው ተተኪዎችን ለማፍራት እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት የዘርፉ ደጋፊ ሀምሳ አለቃ እንየው መላኩ ናቸው።
በልጅነታቸው በሩጫው ትልቅ ቦታ ለመድረስ የነበራቸውን ህልም በተለያየ ምክንያት ባይሳካላቸውም ሌሎችን ለማብቃት ለአሰልጣኝና ሰልጣኞች ለትጥቅና ላብ መተኪያ በወር እስከ 50 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ እየደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ለአትሌቲክሱ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ስፖርቱ በሁሉም አካባቢዎች እንዲስፋፋ የሚመለከተው አካል ተገቢው ድጋፍ እንዲያደርግ አመልክተዋል።
የክልሉ ብስክሌት አሰልጣኝ ኢንስትራክተር መሀመድ ኑር ኢንድሪስ በበኩላቸው አካባቢው ከፍተኛ ፍላጎትና አቅም ያላቸው የዘርፉ ስፖርተኞች መገኛ ቢሆንም ትኩረት አልተሰጠውም ብለዋል።
በራሳቸው ተነሳሽነትና ድጋፍ 45 ወጣቶችን መልምለው በማሰልጠን እስከ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ጭምር ኢትዮጵያን መወከል የቻሉ በረከት ወንድሙና ሌሎችንም ተወዳዳሪዎችን ማፍራታቸውን ጠቅሰዋል።
ለብስክሌት ስፖርት ከፍተኛ ዝግጅትና ጉልበት እንዲሁም መወዳዳሪያ ብስክሌት እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ በዘርፉ ያለውን አቅም አውጥቶ ለውጤት ለማብቃት መንግስትና ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደረጉ ጠይቀዋል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ፣ ክልሉ በተለያዩ ስፖርት ዓይነቶች ያለውን አቅም አጉልቶ ለማውጣት የተጀመሩ ስራዎች እንዲጠናከሩ ይሰራል ብለዋል።
በግልም ይሁን በተለያዩ አማራጮች ዝግጅት ላይ ያሉትን ሆነ ፍላጎቱ ያላቸው ስፖርተኞች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የማዘውተሪያ ስፍራና ሌሎችን ግብአቶች ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ አሰታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩላቸው፤ ክልሉ ድጋፍ ከተደረገለት በርካታ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚችል በማሳያነት ጠቅሰው ገልጸዋል።
በቀጣይ እንደ ታደሰ ወርቁና ሂሩት መሸሻ ዓይነት በርካታ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።