የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2016(ኢዜአ)፦የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በተጓዳኝ "ጥናትና ምርምር ለተሻለ ለአቅም ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በተለይም ከትምህርት ተቋማትና በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በቅርበትና በትብብር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል በማሰማራት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ የትምህርት ሴክተር ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በበኩላቸው ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማነት የትምህርት ዘርፉ የላቀ ሚና ይጠበቅበታል ብለዋል።
ለዚህም የትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ልማት ችግር ፈችና ቀጣይነት ያለው ጥናትና ምርምር ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)፤ በትምህርትና ስልጠና ለኢንዱስትሪ ልማት ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ብቁ የሰው ሃብት የማፍራት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት በጥናትና ምርምር እንዲሁም በፈጠራ ቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።