ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 4/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ።

ሻሸመኔ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን 5 ተከታታይ ጨዋታዎች አላሸነፈም። በ4ቱ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በነዚህ 5 ጨዋታዎች 4 ጎሎች ሲቆጠሩበት ምንም ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ክለቡ በ13 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሀድያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። 1 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በግርማ ታደሰ የሚሰለጥነው ሀድያ ሆሳዕና በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ጎሎችን አስተናግዷል።

ሀድያ ሆሳዕና በ31 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው አይዘነጋም።

በ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሀምበሪቾ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን 1 ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው ሀምበሪቾ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በ4ቱ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በነዚህ 5 ጨዋታዎች ሀምበሪቾ 3 ጎሎችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ የሚመራው ሀምበሪቾ በ8 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

መቻል በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ግቦችን ተቆጥረውበታል።

በገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በ44 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በተካሄዱ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ሃዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም