ቀጥታ፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘርፉ በተሰጠው መልካም ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል--አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016(ኢዜአ)፦ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘርፉ በተሰጠው መልካም ዕድል  በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

ከኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎን ለጎን ከሚካሄዱ መርኃ ግብሮች መካከል "የግል ኢንቨስትመንት እና አስቻይ ሁኔታዎች " በሚል የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።


 

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሥራቸው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እና ሊፈቱ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።

ለአብነትም የባንክ ብድር ወለድ ከፍተኛ መሆን እንዲሁም የኃይል አቅርቦት ችግር በተሳታፊዎቹ በስፋት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ አምራች ዘርፉን መደገፍ የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአምራች ዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት እና ወጪ ምርቶችን በማበረታታት  ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ፤ የዘርፉን ተግዳሮት ለመፍታት ተገቢውን ምክክር ማድረግና አስፈጻሚ አካላትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።


 

በዘርፉ የሚታዩ አመለካከቶችን በማስተካከል የዘርፉን አቅም ማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው(ዶ/ር)፤ ባንኩ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በዝቅተኛ የወለድ መጠን የዘርፉን ተዋንያን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው፤ ንግድ ባንክ በከፍተኛ ሁኔታ አምራች ዘርፉን እየደጎመ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።


 

ይህንንም ሲያብራሩ በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ በኃይል አቅርቦት ላይ የራሱን አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፤ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ተቋሙ ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚያስገባቸውን ምርቶች ከአምራች ኢንዱስትሪው እየገዛ መሆኑን ገልጸው፤ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው ኤሌክትሪክ የአምራች ዘርፉ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በቀጣይም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እየተለዩ የሚፈቱበት አግባብ የሚፈጠር መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የዘርፉ ተዋንያን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ መመልከት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በሚጠበቀው ልክ መሥራት አለመቻል ዘርፉን በዋናነት እየፈተነው እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህንን ለማስተካከል ወደ ውስጥ ማየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዘርፉን በማጠናከር የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በመጠቆም አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘርፉ በተሰጠው መልካም ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሚሰጡ ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን በተገቢው መንገድ በመጠቀም ውጤት ለማምጣት መትጋት እንደሚገባ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም