የ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" የዲጂታል ቴሌቶን መርሃ ግብር ነገ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" የዲጂታል ቴሌቶን መርሃ ግብር ነገ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016(ኢዜአ)፦ የ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" 50 ሚሊዮን ብር በአንድ ጀምበር የዲጂታል ቴሌቶን መርሃ ግብር ነገ ይካሄዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" ንቅናቄ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት ከሀገር ውስጥም ከውጭም በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ንቅናቄውን በመቀላቀል ድጋፋቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።
በነገው ዕለትም በ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" ንቅናቄ 50 ሚሊዮን ብር በአንድ ጀምበር ለማሰባሰብ ያለመ የዲጂታል ቴሌቶን መርሃ ግብር ይካሄዳል።
ከጧቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት የሚካሄደው ዲጂታል ቴሌቶን በ10 ሰዓታት ውስጥ 50 ሚሊዮን ብር ከማሰባሰብ ባለፈ ጽዱ ኢትዮጵያን የመገንባት ጥልቅ ዕሳቤ ያነገበ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም በመርሃ ግብሩ ላይ ስለ ጽዱ ኢትዮጵያ ግንዛቤ የሚፈጥሩና አስተማሪ ይዘቶች ይቀርባሉ።
በዕለቱ የንቅናቄው ዓላማ ከህብረተሰብ ጤና ጋር ያለውን ትስስር በተመለከተ የተለያዩ አካላት ማብራሪያ የሚሰጡ ይሆናል።
ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ንቅናቄውን መቀላቀል ስለሚኖረው አገራዊ ፋይዳ ገለጻ ያደርጋሉ።
በንቅናቄው ወደ ባንክ የሚገባውን ገንዘብ በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ግልጽ የማድረግ ስርአት መዘርጋቱ ተጠቁሟል።
በ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" የዲጂታል ቴሌቶን መርሃ ግብር በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የንቅናቄው አካል በመሆን ሰፊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።