ቀጥታ፡

ግዙፏ "አባይ ሁለት" መርከብ ኬኒያ -ላሙ ወደብ ደረሰች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016(ኢዜአ)፦ 60 ሺህ ቶን ማዳበሪያ የጫነችው ግዙፏ "አባይ ሁለት" መርከብ የላፕሴት ማዕከል በሆነው የኬንያ ላሙ ወደብ ጭነቷን ማራገፍ ጀምራለች፡፡

ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን በኢኮኖሚ የማስተሳሰር አላማ ያለው የላፕሴት ኮሪደር ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር የሎጀስቲክ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፣ የኢትዮጵያ የባህር እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር ) እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች የወደቡን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ያለውን የማዳበሪያ ጥያቄ ለመመለስ የወደብ አማራጮችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) መናገራቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡


 

ለመጀመሪያ ጊዜ የላፕሴት ማዕከል በሆነው የኬንያ ላሙ ወደብ ተጓጉዞ የደረሰው ማዳበሪያም የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ 

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ምርት መጠን እያደገ በመምጣቱ የላፕሴት ኮሪደር ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም