በፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ

ቦንጋ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓሪስ ኦሊምፒክ የችቦ ማብራት ንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።


 

ዶክተር አሸብር በዚህን ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በሚካሄደው ኦሎምፒክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀና አሳታፊ ዝግጅት እያደረገች ነው።

ለዚህም  በምትወዳደርባቸው የስፖርት ዘርፎች ከሌሎች ኦሎምፒክ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የኦሎምፒክ እንቅስቃሴን ለማስፋፋት ሕዝናዊ  ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ አንዱ ክልሎች ንቃት የሚሳተፉበትና ድጋፍ የሚያደርጉበት ንቅናቄ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሹ ዓላማው  ከዕቅድ ዝግጅት እስከ ውጤት ተቀራርቦ በመስራት ስፖርቱን ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ እንደሚረዳ ዶክተር አሸብር ገልጸዋል።

''ኢትዮጵያ ለ2024 ኦሎምፒክ ውድድር በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀች ነው''ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ናቸው።


 

ለዚህም "ኢትዮጵያ ትወዳዳር፣ተወዳድራም ታሸንፍ!" በሚል መሪ ሀሳብ አቅምን ለመጠቀም የሚያስችል የተቀናጀ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል ።

ፌዴሬሽኑ ክልሉ ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በክልሉ ያዘጋጀው የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።


 

ክልሉ በስፖርቱ ዘርፍም አገራቸውን የሚያስጠሩ ዜጎች ለማፍራት ድጋፍ  እንደሚሻ ገልጸዋል። 

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው ክልሉ በአትሌቲክስ፣ በውሃ ዋና፣ በብስክሌትና በሌሎች ዘርፎች ያለውን አቅም ለመጠቀም አገራቸውን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከሚመለከታቸው ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በፓናል ውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባላት የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራር አባላት  እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

33ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 በፓሪስ፣ፈረንሳይ ይካሄዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም