ቀጥታ፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይና ባዛር በአርባ ምንጭ ከተማ መካሄድ ጀመረ

አርባምንጭ ፤ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፡- "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሀሳብ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይና ባዛር በአርባ ምንጭ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

አውደ ርዕዩና ባዛሩ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ70 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን አቅርበው እንደሚያስተዋውቁ ተገልጿል።

ከአውደ ርዕዩና ባዛሩ ጎን ለጎን በተዘጋጀ የውይይት መድረክ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የተመለከተ ሰነድ ቀርቦ በጋራ እንደሚመከርበት ይጠበቃል።


 

መርሀግብሩም በተቀናጀ አመራር አምራች ኢንዱስትሪውን በማዘመን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን እውን ማድረግ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድሎችና ማነቆዎችን በመለየት የዘርፉን ዘላቂ ምርታማነት የማረጋገጥ ዓላማም እንዳለው ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ እና የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አዳማ ትንጳዬን ጨምሮ የክልልና የዞን የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና የልማት ባንክ የሥራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም