ቀጥታ፡

2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የችቦ ማብራት ሥነ ሥርዓት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

ቦንጋ፤ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የችቦ ማብራት ሥነ ሥርዓት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

"ኢትዮጵያ ትወዳደር፣ ተወዳድራም ታሸንፍ" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው የፓሪስ የ2024 ኦሎምፒክ ንቅናቄ መርሃ ግብር ዛሬ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ለንቅናቄው በተዘጋጀ የችቦ ማብራት መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የቦንጋ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በንቅናቄው ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ደጋፊዎች ማህበር የተለያዩ ኩነቶችን እያቀረቡ ይገኛሉ።

እንዲሁም የመርሃ ግብሩ አካል የሆነው የ5 ኪሎ ሜትር አጭር ርቀት ሩጫ፣ የብስክሌት፣ የጂምናስቲክስ እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮችና ኩነቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም