የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 03/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 2 ቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በነዚህ 5 ጨዋታዎች 8 ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን በተመሳሳይ 8 ግቦችን አስተናግዷል። ሃዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች በ3ቱ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። 1 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ሲዳማ ቡና በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ሲያስቆጥር 3 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና 30 ነጥቦችን በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ አይዘነጋም።
በሌላኛው የ24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 3 ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ወላይታ ድቻ በ5ቱ ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ግቦች ተቆጥረውበታል። ክለቡ በ28 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል የቀናው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 1 ጊዜ ሲሸነፍ 3 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በነዚህ 5 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 7 ጎሎችን አስተናግዷል። በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በ35 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልቂጤ ከተማን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ መድን ቅዱስ ጊዮርጊስን 1 ለ 0 ረቷል።