ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የሕግ ማዕቀፍ በቅርቡ ተግባራዊ  ይሆናል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016(ኢዜአ)፦ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ  የተመለከተ መመሪያ ዝግጅት ተጠናቆ በቅርቡ ስራ ላይ እንደሚውል የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በነዳጅ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር  የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል ሙሊትና ተያያዥ ጉዳዮችን ባቀፈው ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት አካሄዷል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ እንዳሉት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን በመከላከል ግሪን ኢኮኖሚ ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ ነው።

ይህን ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ መንግስት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ ለማድረግ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአሰራር ምቹነት ከመፍጠር አኳያም ለተሽከርካሪዎቹ ኃይል ማቅረብ፣ ታሪፍ መወሰንና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በመመሪያው ላይ በኢነርጂ ዘርፍ ከተሰማሩ ማህበራትና ከኤሌክትሪክ መኪና አስመጪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ተጨማሪ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ስራ መከናወኑንም በማስታወስ።

ይህ መመሪያ በፍጥነት ጸድቆ ወደ ስራ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ለተግባራዊነቱም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ መንግስት የግል ባለሃብቱ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መስክ እንዲሰማራ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው መመሪያው የግሉ ሴክተር በዘርፉ እንዲሰማራ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም