ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በዘገባዎቻቸው ተደራሽ በማድረግ ኅላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያወች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሚተገበሩ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በዘገባዎቻቸው ተደራሽ በማድረግ ኅላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠየቀ።

ኢትዮጵያ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ስርአት ለመገንባት እየሰራች መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የዓለም ፕሬስ ነጻነት ቀንን "ጋዜጠኝነት በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ውስጥ" በሚል መሪ ሀሳብ አክብሯል።

በመድረኩ የአየር ንብረት ለውጥና የሥነ ምሕዳር መዛባት በዓለም ላይ የደቀናቸው መልከ ብዙ ቀውሶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያላቸውን ወሳኝ ሚና የተመለከተ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ ትግስት ይልማ የአየር ንብረት ለውጥ ብዝሃ ሕይወትን በማመናመንና ሥነ-ምህዳርን በማዛባት በዓለም ላይ የከፋ አደጋ መደቀኑን ገልጸዋል።

ቢሊዮኖችን ለመልከ ብዙ ቀውሶች እየዳረገ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ እና ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ስለሚወሰዱ የመፍትሔ አማራጮች መረጃን ተደራሽ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ትልቅ ኅላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ጨምሮ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ላይ በምታከናውናቸው ተግባራት መገናኛ ብዙሃን ቀላል የማይባል ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።   

በቀጣይም በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በአካባቢ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ወቅታዊና ሁሉን አቀፍ ግንዛቤን ለማጎልበት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

  

በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ዳሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶናውዝ በበኩላቸው በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች ላይ ቁጥጥርን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል። 


 

በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህሩ አየለ አዲስ (ዶ/ር) የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለው ተጽእኖ፣ መንስኤዎች እና የመፍትሔ እርምጃዎች ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች ውስንነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ጉዳይ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ይህንን ከግምት ያስገቡ መፍትሄ ተኮር ዘገባዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች መሆኑን ጠቅሰው መፍትሄው የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቋቋም ሂደት የዜጎችን ተሳትፎ ለማሳደግ መገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ በመፍጠር ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። 

  

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ኤልያስ ኩሩ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ስርአት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለመጪው ትውልድ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ስርዓት ለማስተላለፍ ሚዲያው የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል።

 የአለም ፕሬስ ነጻነት ቀን በአለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ የተቀመጠውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማክበርና ማስከበር እንደሚያስፈልግ መንግስታትን ለማስታወስ የሚዘከር ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም