ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለፀ።
በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በ2015 በጀት ዓመት በታክስ ሕግ ተገዢነታቸው የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷል።
በዚህ ወቅት የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ ያስፈልጋል።
ሚኒስቴሩ እነዚህን አጣጥሞ ለመሄድ ገቢ አሰባሰቡን የሚያሳድጉ የአሰራር የማሻሻያ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚሰበሰበው የገቢ መጠንም እንዲሁ ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ ቢሆንም፤ ከኢኮኖሚያዊ አቅምና ከወጪ ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ነው ያስረዱት።
በመሆኑም ከፖሊሲ ማዕቀፎች፣ ከታክስ አስተዳደር ሥርዓት እንዲሁም የታክስ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን ክፍተቶችን ከመሙላት አኳያ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ለዓብነት አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎች የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ማሳለጥ እንዲችሉ ጥረት እየተደረጉ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
ከታክስ አስተዳደር አኳያም እንዲሁ የታክስ ህጎች፣ ደንቦችና አዋጆችን ዙሪያ የግብር ከፋዩ ግንዛቤ ለማሳደግ በሥልጠናና በሌሎች መንገዶች ግንዛቤ መፍጠርና በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ እንደሚጠናከር ጠቁመዋል።
በሚኒስቴሩ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደሰ፣ የታክስ ህጎችን ከማስከበር ባሻገር፤ ግብር ከፋዮች ግዴታና መብታቸውን የማሳወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ግብር ከፋዮች በታክስ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በሚገባ እንዲረዱ ተከታታይና ወጥነት ያለው ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በህግ ተገዢነት መስፈርት የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ግብር ከፋዮች እውቅና ሲሰጥ ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፣ በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው 24 ግብር ከፋዮች ዕውቅና እንዳገኙ አስታውቀዋል።
በቅርንጫፉ በ2015 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 383 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 3 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ደግሞ 2 ነጥብ 54 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ባለፉት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሳወቅ የቻሉ ሲሆን፣ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መፈጸሙን አስረድተዋል።
እውቅና ከተሰጣቸው ግብር ከፋዮች መካከል በ2015 በጀት ዓመት ከ652 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የከፈለው የዘቢዳር ቢራ ፋብሪካ አስተዳደር አቶ ዳዊት ጠጄ፣ ፋብሪካው የታክስ ህጎችን ተከትሎ በወቅቱ አሳውቆ እንደሚከፍል ተናግረዋል።
'ግብርን በአግባቡ መክፈል ሀገራችንን የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሳ እንድናያት የሚያስችል በመሆኑ በታማኝነት መክፈላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን'' ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በበጀት ዓመቱ 251 ሚሊዮን ብር ግብር በመክፈል ዕውቅና የተሰጠው ሌላው ድርጅት ደግሞ አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሲሆን፣ የፋብሪካው ተወካይ ሀጂ አማኖ ኤዳዎ ድርጅቱ ገቢን የሚያሳውቅና የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ የሚከፍል ነው ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የሚኒስቴሩና የሀዋሳ ቅርንጫፍ እንዱሁም ክልል ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ሥልጠና ወስደው ለምረቃ የበቁ ግብር ከፋዮች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።