ተቋርጦ የነበረው የብሔራዊ የደረጃዎች የምልክት ክፍያ ስርዓት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተቋርጦ የነበረው የብሔራዊ የደረጃዎች የምልክት ክፍያ ስርዓት ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦ ተቋርጦ የቆየውን የብሔራዊ ደረጃዎች የምልክት ክፍያ ስርዓት በቀጣይ አመት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በብሔራዊ የደረጃ የምልክት አጠቃቀምና የክፍያ ስርዓትን ዳግም ለማስጀመር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የብሔራዊ የደረጃዎች የምልክት ክፍያ ስርዓት፤ የአገር ውስጥ አምራቾች ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግም የሚያግዝ እንደሆነም ተጠቁሟል።
ብሄራዊ የደረጃዎች ምልክት አምራቾች የምርታቸውን ጥራትና አገልግሎት ለደንበኞቻቸው ለማስተዋወቅ የሚረዳ ሲሆን ሸማቹ ማሕበረሰብም የምርት ጥራትን በቀላሉ እንዲገነዘብ የሚያደርግ መሆኑንም እንዲሁ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያና በአፍሪካ የንግድ ቀጣና ለማቅረብ እንድትችል እየተሰራ ነው።
ከዚህ ውስጥም የአስራር ስርዓቶችን የማሻሻል፣ በቴክኖሎጂ የመደገፍ፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በተለያዩ ምርቶች ላይ አዳዲስ ብሄራዊ የደረጃዎች ምልክት በማውጣት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በተቋማት አደረጃጀት ሳቢያ ተቋርጦ የነበረው የብሔራዊ የደረጃዎች ምልክት የክፍያ ስርዓትን ዳግም ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተደረገ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ የደረጃዎች ምልክት የክፍያ ስርዓት መጀመር መንግስት ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያገኝና የአገር ውስጥ አምራቾች ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዲሪባ ኩማ፤ በበኩላቸው ብሄራዊ የደረጃዎች ምልክት በግብርናው ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለተጠቃሚው ለማቅረብ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ጥራት የሌለው ምርትም ለገበያ የሚያቀርቡ አምራቾችንም ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በ50 ዓመታት ውስጥ 11 ሺህ 890 ያክል አጠቃላይ ደረጃዎችን ያወጣ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 350 ደረጃዎችን በአስገዳጅነት ማፅደቁን መረጃዎች ያሳያሉ።