የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ለውጪ ገበያ የማቅረብ ዕድል ፈጥሯል - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ለውጪ ገበያ የማቅረብ ዕድል ፈጥሯል - አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦ የተኪ ምርቶች ስትራቴጂን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕድል መፍጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀውን ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ትናንት በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡
ኤክስፖው ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
በዛሬ ዕለትም በኤክስፖው ተወዳዳሪነት ለሀገር ዕድገት፤ ገቢ ምርትን በጥራት መተካት በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የኢትዮጵያን ምርቶች በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተከናወኑ ስራዎች ተዳሰዋል፡፡
በሌላ መልኩ የሀገር ውስጥ ምርትን ከማስተዋወቅ፣ የምርት ጥራት ደረጃዎችን ከማሻሻል እና የምርት ብራንዲንግ ጥረቶችን ከማዳበር አኳያ የተከናወኑ ስራዎች እና ቁልፍ የፖሊሲ መስኮች በውይይቱ ተዳሰዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የስራ እድል ከመፍጠር እና የኑሮ ሁኔታን ከማሻሻል ባሻገር የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዘርፉ ጠንካራ መሰረት ያለው የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው በመንግስት በኩል ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ ከአገራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር የተቀናጀ አሰራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል፡፡
የተኪ ምርት ስትራቴጂ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው እስከአሁን 96 ምርቶችን በመለየት በአገር ውስጥ የመተካት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ስትራቴጂው ተግባራዊ በመደረጉ አንዳንድ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ ለአብነትም የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ እና የቢራ ብቅልን ጠቅሰዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ለውጪ ገበያ የማቅረብ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው አሁን ላይ የተለያዩ ምርቶቹ ለጎረቤት ሀገራት እየተላኩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
መንግስት የተኪ ምርቶች ስትራቴጂን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ በግብዓት ፣ በመሰረተ ልማት እና በአሰራር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ተኪ ምርቶችን በተመለከተ ከዲዛይን ጀምሮ በአጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ሂደት ጥራት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ይህም ምርቶች አስተማማኝ እና የደንበኞችን ደህንነት በመጠበቅ ተመራጭ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አምራቾች በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እና ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በብቃት ለመወዳደር ለጥራት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት የምርት ጥራትን ከተወዳዳሪ ዋጋ ጋር ማመጣጠን አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
መንግስት ጥራት ያላቸው ምርቶች ወደ ገበያ እንዲቀርቡ የምርት ጥራት መፈተሻ መሰረተ ልማቶችን በልዩ ትኩረት እየገነባ መሆኑን ጠቁመው የንግድ ፖሊሲ እና ብሔራዊ የጥራት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል መላኩንም ነው የጠቆሙት፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ኢንዱስትሪ በሀገር እድገት ላይ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ “ዩኒቨርሲቲ ለኢንዱስትሪ” በሚል መሪ ሃሳብ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ልዩ የስልጠና መርሃ ግብሮችን በመዘርጋት በእውቀትና በክህሎት የዳበሩ ምሩቃን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አምራቾች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
መንግስት ወደ ሀገር ውስጥ ከሚያስገባቸው 262 መድኃኒቶች ውስጥ 97 የሚሆኑት በሀገር ወስጥ እየተመረቱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።