ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ውሃ አዘል መሬቶችን ዘላቂ አጠቃቀምና ልማትን የተመለከተ ፖሊሲና አዋጅ ሊወጣ ነው- የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ውሃ አዘል መሬቶች ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል የውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀምና ልማት ፖለሲና አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

በኢትዮጵያ ውሃ አዘል መሬቶች በእርሻ ስራ፣ በግጦሽ እና በሌሎች ተግባራት ችግር ውስጥ እየገቡ እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

የውሃ አዘል መሬቶች ለሐይቆች፣ለወንዞችና ምንጮች፤ የፍሰት መጠን እና ጥራት ሕልውና ዋስትና ሲሆኑ በሌላ በኩል ለአካባቢ ሥነ-ምሕዳርና የተፈጥሮ ሚዛን በመጠበቅ አይተኬ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል። 

ከዚህ አኳያም የዘርፉ ምሁራን የውሃ አዘል መሬቶች ከአደጋ ለመጠበቅና ተገቢውን የአጠቃቀም ስርዓት ለመተግበር የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልጋቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይስተዋላል። 

ጉዳዩ የሚመለከተው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንም የውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም፣ እንክብካቤና ልማት የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

በባለስልጣኑ የውሃማ አካላትና ውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም፣ ክትትልና ቁጥጥር ዴስክ ሀላፊ አቶ ዘሪሁን መንገሻ እንዳሉት ውሃ አዘል መሬቶች ለውሃ ሀብት መጎልበትና ዘላቂነት ዋስትና እንደሆኑ አንስተዋል።

ከሀገር ውስጥ የውሃ ሀብት ጥበቃ ባሻገርም ለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍሰትም ሁነኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የውሃ አዘል መሬት አጠቃቅምና ልማትን የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ውሃ አዘል መሬቶች የሚመሩበት የአሰራር ስርዓት እና የሚዳኙበት ረቂቅ ፖሊሲ እና አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

የሕግ ማዕቀፉ ተግባራዊ ከተደረገ የውሃ አዘል መሬቶች መመናመንና መጎዳት ሳቢያ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያርፍባቸው የውሃማ አካላትን ብክለት እና ስነ ምህዳር መመናመንን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በአካባቢ ጥበቃና ልማት ላይ የምታከናውናቸውን ስራዎች ለውሃ አዘል መሬቶች ደህንነት እና ለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍሰት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የውሃ ምንጭ በመሆኗ ለዘላቂ የተፋሰስ ልማት እና የውሃ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን ሀገራቱ ማገዝ እንደሚገባቸው አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም