መንግስት የወጪ ንግድን ከማስፋት በተጓዳኝ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የወጪ ንግድን ከማስፋት በተጓዳኝ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016(ኢዜአ)፡- መንግስት የወጪ ንግድን ከማስፋት በተጓዳኝ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀውን ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ትናንት በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
በዛሬ ዕለትም በኤክስፖ ተወዳዳሪነት ለሀገር ዕድገት፤ በምርት ጥራት ገቢ ምርትን መተካት በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤መንግስት የወጪ ንግድን ከማስፋት በተጓዳኝ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ለዚህ ደግሞ የተኪ ምርት ስትራቴጂ በማዘጋጀትና 96 የሚደርሱ ምርቶችን በመለየት በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስትራቴጂው ተግባራዊ መደረጉ አንዳንድ ምርቶች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት ማስቻሉን ገልፀው፤ ለአብነትም የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ እና የቢራ ብቅልን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ብለዋል።
ምርቶቹ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
መንግስት የተኪ ምርቶች ስትራቴጂን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ በግብዓት ፣ በመሰረተ ልማት እና በአሰራር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡