ክልሉን ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኮሪደር ለማድረግ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉን ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኮሪደር ለማድረግ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016(ኢዜአ)፡- ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የሀገሪቱ ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኮሪደር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት መሻገር የሚያስችሉ ትክክለኛ የልማት ፖሊሲዎች እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ለውጥ መምጣቱንም አንስተዋል።
በተለይ በበጋ መስኖ የስንንዴ ልማት ኢትዮጵያን ከልመና የሚያላቅቅና ለአህጉሪቱ ምሳሌ የሆነ አዲስ ታሪክ መጻፉን ነው የተናገሩት።
ደቡብ ኢትዮጵ ክልልም እንደ ሀገር የታቀዱ የልማት ግቦችን ለማሳካት በበጋ መስኖ በተለይም በቋሚ ሰብል ልማት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።
ክልሉ ለመስኖ ልማት የሚውል ሰፊ መሬት እና ትላልቅ ወንዞች ያሉት መሆኑም የመልማት እድሉን እንደሚያሰፋው ጠቅሰዋል።
ይህንን እምቅ አቅም በመጠቀም ክልሉን የአትክልትና ፍራፍሬ የልማት ኮሪደር ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ክልሉ በሙዝ፣ በአቮካዶ፣ በማንጎ እና በደጋ አፕል ምርቱ እንደሚታወቅ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።
ከሙዝ ልማት ብቻ በሄክታር ከ300 እስከ 400 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የሌሎች ፍራፍሬዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ልዩ የኤክስቴንሽን መርሐ ግብር ወጥቶ በመተግበር ላይ ነው ብለዋል።