የሱፐርቪዥን ቡድኑ የመስክ ምልከታ የኢትዮጵያ ትክክለኛና ተስፋ ሰጪ የብልጽግና ጉዞ ያመላከተ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የሱፐርቪዥን ቡድኑ የመስክ ምልከታ የኢትዮጵያ ትክክለኛና ተስፋ ሰጪ የብልጽግና ጉዞ ያመላከተ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- በፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የመስክ ምልከታ የኢትዮጵያ ትክክለኛና ተስፋ ሰጪ የብልጽግና ጉዞ ያመላከተና መልካም ተሞክሮ የተገኙበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
መንግስት ያቀደው የ10 ዓመት የልማት ግብ እንዲሳካ የፌዴራል ተቋማት ያሳዩት አፈጻጸም አመርቂ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ባለፉት 15 ቀናት በፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን በተካሄደው የመስክ ምልከታ የማጠቃለያ ሪፖርት መርሃ ግብር ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የ10 ዓመቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ሶስት የዕቅዱ ትግበራ ዓመታት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መልካም ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በፌዴራል ተቋማት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ግብን ለማሳካት የሚረዱ መሆናቸውን ጠቁመው በፌዴራል ተቋማት የተደረገው ሱፐርቪዥን ይህን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የመስክ ምልከታ በወረቀት ከሚመጣው ሪፖርት ባሻገር መሬት ላይ ያለውን እውነት ያሳየ መሆኑን ጠቁመው መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት እንዲሁም ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
የሱፐርቪዥን ስራው በ207 አባላት 27 ቡድኖች መከናወኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ28 ተቋማት ላይ ትኩረት በተደረገባቸው 39 ጉዳዮች ዙሪያ ምልከታ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ተቋማት አሰራራቸውን ለማዘመን የሄዱበት ርቀት በመልካምነት የሚገለጽ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ ሱፐርቪዥኑ ከለውጡ ወዲህ የመጡትን አንኳር ተግባራት ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም ምርታማነት፣ ጥራት እና ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ አንጻር አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ አሻራ የተከናወኑ ስራዎች አመርቂ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣ ለውጪ ገበያ የማቅረብ እና ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻርም ተምሳሌት የሚሆኑ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው መንግስት ያቀደውን የ10 ዓመት የልማት ግብ ማሳካት የሚያስችሉ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በሱፐርቪዥኑ የተመላከተውም ይህንኑ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው ተቋማት ያሳዩት አፈጻጸም አመርቂ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፤ ተቋማት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመሩት ስራ ጥሩ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት የግዢ አገልግሎት እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራትም ለዚሁ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ ተቋማት መረጃዎችን በማደራጀት ለመገናኛ ብዙሃን የመስጠት ኋላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው የተቋማት መልካም አፈጻጸም ኢትዮጵያ በብልጽግና ጎዳና ላይ ለመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡