በምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት ውህደትን ለማፋጠን የፋይናንስ ዘርፍ ትስስርን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት ውህደትን ለማፋጠን የፋይናንስ ዘርፍ ትስስርን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- በምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት ውህደትን ለማፋጠን የፋይናንስ ዘርፍ ትስስርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
አይካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ሰባተኛው የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የኬንያ ሰኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍራንክ ሊኦይድ፤ በቀጣናው ጠንካራ ምጣኔ ኃብት ለመገንባት ትብብርን ማጠናከር ቁልፍ መሆኑን ገልፀዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባዔ ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል።
ስትራቴጂክ አጋርነትን በማጠናከር፣ በመሠረተ-ልማት፣ በአካታችነት፣ በኢንቨስትመንት ዕድሎችና ሌሎች ዘርፎች በትብብር መሥራት አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ በኢኮኖሚው ላይ እያደረገች ያለው ሪፎርም የሚበረታታ እርምጃ መሆኑንም ገልፀዋል።
በጎረቤት ሀገራት የሚደረጉ የምጣኔ ኃብት ለውጦች በቀጣና እንዲሁም በአህጉሩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋጽዖ በመረዳት በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ ሪፎርም እያደረገች መሆኑን ገልፀዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስጋቶችን መቋቋምና ምላሽ መስጠት የሚያስችል፣ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር ብሔራዊ ባንክ እየተገበራቸው ከሚገኙ ስትራቴጂዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተደራሽነት፣ አካታችነት፣ ዲጂታል ፋይናንስ፣ አገልግሎት ስብጥር፣ በዘመናዊ የስጋት አስተዳደር ተጨባጭ ለውጥ መገኘቱንም ገልፀዋል።
በዘርፉ በተመዘገበ እድገት አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማት 121 የደረሱ ሲሆን፤ ኃብታቸውም 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር መድረሱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ተቀማጭ ገንዘብ 2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር እንዲሁም የብድር መጠን 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር መድረሱን አቶ ማሞ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ እያከናወነች ካለው ተግባር ባሻገር የካፒታል ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ተወዳዳሪነትን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን ያነሱት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄሉ ዑመር(ዶ/ር) ናቸው።
በዓለም ላይ የፋይናንስ ዘርፉ እንዲሁም የካፒታል ገበያ በፍጥነት እያደጉ ቢሆንም በሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ በቴክኖሎጂ አቅም፣ በዋጋ ግሽበትና የሰላም እጦት ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የፋይናንስ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ትብብርን ማጠናከር ቁልፍ መሆኑን በማንሳት፤ ዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል በማፍራትና በጥናትና ምርምር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአይካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚና የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባዔ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገመቹ ዋቅቶላ፤ ጉባዔው በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና ትብብርን ለማጠናከር ዕድል እየፈጠረ ነው።
ተለዋዋጭ ከሆነው የፋይናንስ ዘርፍ ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ የሚቀጥል የዘርፉን ተዋናይ ማዘጋጀትና ወደ ፓን-አፍሪካ ጉባዔ ማሳደግ ቀጣይ ትኩረቶች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ሰባተኛው የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባዔ የዘርፉን ውጤታማነትና ትብብርን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ነገም ይቀጥላል።