ቀጥታ፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው ስትራቴጂክ በሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው ስትራቴጂክ በሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስታወቀ።

ቶፓን ግራቪቲ ኢትዮጵያ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፓስፖርት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የኤ ቲ ኤም ካርድና መሰል የደኅንነት ሕትመቶች ማምረቻ ለመገንባት በትላንትናው እለት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በዛሬው እለትም ፋብሪካው በሚያከናውናቸው ስራዎች ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ መልዕክት ሳህሉ በዚሁ ወቅት፤ የምስጢራዊ ህትመቶች ፋብሪካ በመንግስትና በግል አጋርነት የሚከናወን የመጀመሪያው ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ስትራቴጂክ የሆኑ ቅድሚያ በሚሰጣቸው በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንጅነሪንግ፣ በሎጀስቲክስ በዲጂታላይዜሽን እንዲሁም ቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ላይም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመጣመር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የንግድ ምህዳሩ ላይ መተማመን እንዲጨምር እና ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች መሬት ላይ እንዲወርዱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እንዲሁ።

የቶፓን ግራቪቲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቃልኪዳን አረጋ ድርጅቱ የጃፓኑ ቶፓን ግራቪቲ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ እንዲሁም የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ በጋራ ያቋቋሙት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዋናነትም ምስጢራዊ ህትመቶችን ለማተም የተቋቋመ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ ህትመቶች ከሀገር ውጭ እየታተሙ ሲመጡ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።

ፋብሪካው በኢትዮጵያ መገንባቱ ምስጢራዊ ህትመት ውጤቶች አቅርቦትን ከማሻሻል ባሻገር የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚያስቀር ስለመሆኑንም ተናግረዋል።

በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።

ፋብሪካው በዓመት 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ፓስፖርቶችን እንደሚያመርትና ከሀገር ውስጥ ባለፈ የውጭ ሀገራት ፍላጎትን የሚያስተናግድ ሆኖ እንደሚገነባም ገልጸዋል።

የቶፓን ግራቪቲ የግብይት ምክትል ፕሬዝደንት አንቱዋን ቶጊ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ትልቅ ገበያ እንዳላት አብራርተዋል፡፡


 

ይህም ኩባንያው ኢንቨስት ለማድረግ እንዲመርጣት ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታዋቂ አየር መንገድ ባለቤት መሆኗም ሌላኛው ለምርጫ ያበቃት መሆኑንና ይህም ከአፍሪካ ውጭ ባሉ የአለም ሀገራት ተደራሽ መሆን የሚያስችላት መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ይህንን ማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም