ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውይይትና መደማመጥ ልምድን በማጎልበት ጠንካራና የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የውይይትና መደማመጥ ልምድን በማጎልበት ጠንካራና የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው አራተኛው ልዩ አውደ-ጥናት የኢትዮጵያ አብዮት ከ50 ዓመት በኋላ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትሩፋቶቹና የተሸጋገሩ እዳዎች በሚል ርዕስ ተካሂዷል።

በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የተለያዩ ምሁራን እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትሩፋቶችና የተሸጋገሩ እዳዎችን በተመለከተ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል።


 

በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ የአሁኑ ትውልድ የተሻገሩ እዳዎችን ለማለፍ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የውይይትና መደማመጥ ልምድን በማጎልበት ጠንካራና የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ ነው ሲሉም አንስተዋል። 

ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል፤ የአሁኑ ትውልድ በድህነት ላይ ተረባርቦ በመዝመት ሀገሩን ነፃ ማውጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ስኬት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ለማበርከት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅነት የሚካሄዱ የውይይት መድረኮች ለፖሊሲ ግብዓት፣ ለሀገራዊ ልማትና እድገት የላቀ አስተዋጽዖ እያደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በኮሌጆች ከሚደረጉ ውይይቶችና አውደ-ጥናቶች በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እንድምታና ትርጉም ያላቸው መድረኮች ሲዘጋጁ ቆይቶ የዛሬው አራተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የዛሬው የውይይት መድረክ ከ50 ዓመታት በፊት በተካሄደ አብዮት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ በሀገራዊ ምክክር ተሞክሮና ጠቀሜታ፣ የአድዋ ድል እንድምታ ላይ መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

የውይይት መድረኮቹ ለፖሊሲ ግብዓትና ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የላቀ አስተዋጽዖ እያደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም