የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ላይ ያላቸውን ድርሻ አሻሽሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ላይ ያላቸውን ድርሻ አሻሽሏል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ላይ ያላቸው ድርሻ እንዲሻሻል ማድረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን በዛሬው እለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎችን ይዞ በሚያዚያ 2014 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።
የሀገር ውስጥ ምርትና አምራቾችን ማጠናከር፣ መሪ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ መገንባት፣ ጥናትና ምርምርን ማሳደግ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስ ከባቢን መፍጠር ደግሞ የንቅናቄው የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ዘርዝረዋል፡፡
ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ባሉ ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ያስመዘገቡ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የንቅናቄውን የትኩረት አቅጣጫዎች በመተግበር የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ 56 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
ዘርፉ በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ላይ ያለው ድርሻም አሁን ላይ 39 በመቶ መድረሱን ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡
በዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መሰረት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ ኤክስፖዎች ከ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ጠቁመዋል፡፡
በዛሬው እለት የተከፈተው ኤክስፖም መሰል ትስስሮችን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።