ፌዴሬሽኑ በ12 ክልሎች የሚገኙ ጤና ተቋማትን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሚያደርግ ግንባታ መጀመሩን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴሬሽኑ በ12 ክልሎች የሚገኙ ጤና ተቋማትን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሚያደርግ ግንባታ መጀመሩን ገለጸ
አዳማ ፣ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባገኘው ድጋፍ በ12 ክልሎች የሚገኙ ጤና ተቋማትን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሚያደርግ ግንባታ መጀመሩን ገለጸ።
ፌዴሬሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር በክልል የሚገኙ ጤና ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ በማድረግ ላይ ያተኮረ የውይይት መርሃ ግብር ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በአብዛኛው የጤና ተቋማት ሆነ ሌሎች አገልግሎት መስጫ ህንፃዎች የአካል ጉዳተኞችን ችግር ከግንዛቤ ያስገቡ አይደለም።
በአንዳንድ ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኛ መወጣጫዎች ተብለው የሚሰሩ ደረጃዎች ጥራታቸውን ያልተጠበቁና ለባሰ አደጋ የሚያጋልጡ ሆነው እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ፌደሬሽኑ ችግሩን ለማቃለል ለአንድ ዓመት ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለአገልግሎት መስጫ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ምሳሌ ለመሆን ፕሮጀክት ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የጤና ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተደራሽነት ለማረጋገጥ በ12 የክልል ከተሞች ጤና ተቋማት ምቹ የመሰረተ ልማት ግንባታ በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክቱ በአካል ድጋፍና በዊልቸር ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞች ምቹ ደረጃ መወጣጫዎች (ራምፖች) መሆኑንም አቶ ዓባይነህ አስታውቀዋል፡፡
የአዳማ ከተማ ጤናና ጤና ነክ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ሮባ በበኩላቸው በከተማዋ ያሉት የመንግስትም ሆኑ የግል የጤና ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ምቹ አለመሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጤና ተቋማት ምቹና ተደራሽ እንዲሆኑ የጀመረው ስራ ለሌሎች መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የጤና ተቋማቱ ለአካል ጉዳተኞች አካታች አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያግዝና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እውን እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት አቶ መሐመድ ያሲን በሰጡት አስተያየት በጤና ተቋማት የደረጃ መወጣጫና አገነባብ ሁኔታ የአካል ጉዳተኛውን ተጠቃሚነት ያገናዘቡ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች በጤና ተቋማት ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችላቸው መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ለበርካታ ችግሮች እንደሚዳረጉ ገልጸዋል፡፡
እሳቸውም አካል ጉዳተኛ እንደመሆናቸው አልፎ አልፎም ለባሰ አካል ጉዳት የሚያጋልጡ የደረጃ መወጣጫዎች እንደሚያጋጥሟቸው አክለዋል፡፡
አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሆነው እንዲገነቡ የሚያስገድደው ዓዋጅ ተፈፃሚነት እንዲኖረው የባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡