ቀጥታ፡

የሶማሌ ክልል ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- የሶማሌ ክልል  ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት  አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ የሚያደርግ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ኢብራሔም ኡስማን ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በእስካሁኑ ሂደትም ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የተሳታፊዎች ልየታ በማድረግም አጀንዳ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ተግባራትን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በሂደቱ የሕዝቡ ተሳትፎና እገዛ እንዳለ ሆኖ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራትና ሌሎችም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ኢብራሔም ኡስማን፤ የክልሉ መንግስት ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ኮሚሽኑ ለሚያደርገው ጥረት ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከስራው ጋር በተገናኘ በየደረጃው ካሉ አመራሮች፣ ኡጋዞችና የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል።

በመሆኑም በክልሉ ለምክክር ኮሚሽኑ ስራዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የተሳካ የምክክር ሂደት እንዲኖር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል። 

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሰው ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረትም ክልሉ የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ በምክክር ሂደት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም