ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። 

ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከነማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 1 ጊዜ ሲሸነፍ 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ፋሲል ከነማ በነዚህ 5 ጨዋታዎች 6 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ 6 ጎሎችን አስተናግዷል።

ክለቡ በ36 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ባለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። 3ቱን ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ባህር ዳር ከተማ በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በ40 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል፤ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 4 ጎሎችን አስተናግዷል።

በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚሰለጥነው ድሬዳዋ ከተማ በ33 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 3ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል፤ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

አዳማ ከተማ በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 3 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ በ37 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።

የ24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ወልቂጤ ከተማ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ47 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

ሻሸመኔ ከተማ በ13 እና ሀምበሪቾ በ8 ነጥብ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌማን በ13 ግቦች እየመራ ነው። የመቻል አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ በ12 የባህር ዳር ከተማው ቸርነት ጉግሳ በ11 ጎሎች ይከተላሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም