የምስጢራዊ ህትመቶች ፋብሪካ በኢትዮጵያ መገንባት የዲጂታላይዜሽን ጉዟችንን ወደ ተሻለ ምእራፍ የሚያሸጋግር ነው - አህመድ ሸዴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- የምስጢራዊ ህትመቶች ፋብሪካ በኢትዮጵያ መገንባት የዲጂታላይዜሽን ጉዟችንን ወደ ተሻለ ምእራፍ ያሸጋግራል ሲሉ  የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሸዴ ተናገሩ፡፡

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ  የፓስፖርት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የኤ ቲ ኤም ካርድና  መሰል ምስጢራዊ ሕትመቶች ማምረቻ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

ፋብሪካው የጃፓንና የኢትዮጵያዊያን አጋሮች የመሰረቱት ቶፓን ግራቪቲ በተሰኘ ኩባንያ የሚገነባ ነው፡፡


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አገሪቱን በተለያዩ ዘርፎች ወደ ፊት የሚያራምዱ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው የምስጢራዊ ህትመት ፋብሪካም ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን ወደ ዲጂታላይዜሽን የሚደረገውን ጉዞ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ ጥቂት ወራትም ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ፕሮቶኮል ጋር በተጣጣመ መልኩ ማይክሮ ቺፕ ያለውን ፓስፖርት በአገር ውስጥ በማምረት ተደራሽ የማድረግ ስራ እንደሚከወን ገልጸዋል።

ይህ የምስጢራዊ ህትመት ፋብሪካ ከሰነድ ማምረት ያለፈ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደፊት የሚያራምድ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን በምስጢራዊ ህትመት ከአፍሪካ ቀዳሚ በማድረግ  ለውጭ ምንዛሪ ግኝት በር ከፋች መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው፤ ቶፓን ግራቪቲ 120 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ የጃፓን የሕትመት ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል።

በ137 አገራትም በምስጢራዊ ሕትመት ዘርፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የሚገነባው ፋብሪካም  በአፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። 


 

ፋብሪካው በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የፓስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ናቸው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶችን በስብጥር እንዲያመርቱ በርካታ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የምስጢራዊ ህትመቶች ፋብሪካም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም