በጎንደር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 50 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል- ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡-  በጎንደር ከተማ ሰላምን ሙሉ በሙሉ ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 50 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ገለጹ።

በከተማዋ የበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የሰላም ችግር  በፀጥታ አካላትና በህብረተሰቡ  ርብርብ መቀረፉንና ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ፍፁም ሰላማዊ መሆኗን ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ሰፊ ትኩረት መስጠቱን  ጠቅሰው በሚያዚያ ወር ብቻ በአምራች ዘርፉ 46 ባለሃብቶች የልማት መሬት መረከባቸውን ገልጸዋል።

የመሠረተልማት ማሟላት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም  ነው ያነሱት።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 210 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬት የአካባቢው ሰላም መሆን ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

ባለሃብቶቹ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ እና በሪልስቴት ዘርፍ ነው ፈቃድ የወሰዱት። 

የቅባት እህሎች፣ ጥጥና ሌሎች የሚመረቱበት የልማት ኮሪደር በመሆኑ ጎንደር ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሆናለች ነው ያሉት።

የከተማ አስተዳደሩ አመራር ሰላምን ከማፅናት ባለፈ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በከተማዋ ከዚህ ቀደም ተጓተው የነበሩ አብዛኛው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም ከተማዋን የሚያገናኙ የ18  ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ፣ እንዲሁም የ15 ኪሎ ሜትር የኮብል መንገድ  የሶስት ድልድዮች ግንባታ መጠናቀቃቸውን አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከህዝብ ጋር በቀጥታ በማገናኘት የአገልግሎት አሰጣጥ በህዝብ የሚገመገምበት እና ውሳኔ የሚሰጥበት "ከንቲባ ችሎት" የተሰኘ አሠራር መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይም የጎንደርን ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ሥራ ህዝብን ባሳተፈ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም