በክልሉ የአካባቢ ብክለትን የመከላከል ሥራ በተደራጀና ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ ነው

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የአካባቢ ብክለትን የመከላከል ሥራ በተደራጀና ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ።

"ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር ሲካሄደ የቆየው ክልል አቀፍ የፕላስቲክ ቆሻሻ የፅዳት ዘመቻ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት በባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ቲቦ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ከፕላስቲክ ቆሻሻ የፀዳ አካባቢን ለመፍጠር በ37 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ህዝብን ያሳተፈ ንቅናቄ በዘመቻ እየተካሄደ ነው። 


 

በዚህም ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ተግባራዊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ በዛሬው መርሀ ግብርም የሀዋሳ ሐይቅን ከፕላስቲክ ብክለት የመከላከል ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ እየተከናወነ ያለው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በዚህም የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈር እና የድምጽ ብክለትን በመከላከል የአካባቢና የማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ይካሄዳል ብለዋል።

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ በተለይ የሀዋሳ ሐይቅን ከቆሻሻ ብክለት፣ ከጎርፍና ከደለል አደጋ በዘላቂነት ለመከላከልና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሐይቁ ዙሪያ የቆላ ቀርከሃና ተስማሚ የእፅዋት ዝርያዎችን ችግኝ በመጪው ክረምት ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሀዋሳ ከተማ ደን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አረጋ ባርሴ በከተማዋ ለአካባቢ ብክለት መንስኤ የሆነ ቆሻሻ በከፍተኛ ሁኔታ ይመነጫል።


 

ችግሩን ለማቃለል ህብረተሰቡን፣ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎችን በማስተባበር ጠንካራ የአካባባቢ ጥበቃ ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉትና በሀዋሳ ከተማ ጢሊቴ ቀበሌ የአካባቢ ጥበቃ ልማት ማህበር አባል ወይዘሮ መሰለች መልኬ፣ ማህበሩ 114 ወጣቶችን በማቀፍ ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይ ሀዋሳ ሐይቅ ከተጋረጠበት የብክለት አደጋ ለመታደግ በሳምንት ሁለት ቀናት የፕላስቲክ ቆሻሻን ከሐይቁ ላይ በዘመቻ እያነሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የሀዋሳ ሐይቅ አሣ አስጋሪዎች ማህበር ሊቀመንበር ሉቃስ ካንቼ በበኩሉ "የሀዋሳ ፍቅር ሐይቅ በተፈጥሮ የተሰጠን የጋራ ሀብታችን ነው" ብሏል።


 

ይሁን እንጂ ከከተማዋ በየጊዜው ወደሐይቁ የሚገባው የፕላስቲክ ቆሻሻ ሐይቁን ለብክለት እየዳረገና በአሣ ምርት ላይ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን ተናግሯል።

የማህበሩ 495 አባላትም በየእለቱ ወደ ሐይቁ የሚገቡ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ከውሃው አካል ላይ በማንሳት ሐይቁን ከበክለት ለመታደግ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ነው የተናገረው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መርህ የቆሻሻና ፕላስቲክ ውጤቶች አወጋገድን በማዘመን ጽዱና ውብ አካባቢን የመፍጠር የስድስት ወራት ንቅናቄ መጀመሩ የሚታወስ ነው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም