ኢትዮጵያ እና ተ.መ.ድ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በመደገፍ ረገድ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተ.መ.ድ) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በመደገፍ ረገድ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ የሀገር ውስጥ መፈናቀል መፍትሄዎች ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደቀዬአቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን አብራርተዋል።


 

ሮበርት ፓይፐር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከለላ መስጠትና መርዳት የሚያስችለውን አዋጅ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን እርምጃ አድንቀዋል።

መንግስት በርካታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደመጡበት አካባቢ መመለስ መቻሉን አድንቀው ይህም የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያሳያል ብለዋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው ውይይት በሰብአዊ ድጋፍ ሰጭዎች እና የሰላም ተዋናዮች መካከል ትብብር እና ቅንጅት እንደሚያስፈልግ መጠቆሙን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ውይይታቸውም በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ኢትዮጵያ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት እና መልሶ በማደራጀት ረገድ ሊኖራቸው የሚችለው ትብብር ላይ ያተኮረ እንደነበርም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም