በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ  ወራት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል

ሆሳዕና ፤ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለፁ።

የክልሉ መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ''በትምህርት ለትውልድ'' እና ''አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ'' በሚል በተዘጋጀው የንቅናቄ መርሃ ግብር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ለትምህርት ልማቱ መዋሉም ተመላክቷል። 

መድረኩን የመሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።


 

በቀጣይም ያሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር  የህዝብ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ጥረት  እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ለዚህም የክልሉን ሠላም በማጽናት በሁሉም መስኮች ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የክልሉ መንግሥት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

በተለይ የህዝብ አደረጃጀቶችን መደገፍና ማጠናከር ለተያዘው ግብ መሳካት ወሳኝነት እንዳለው ገልፀው በየደረጃው የሚገኙ አደረጃጀቶች በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱም አሳስበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላም ኦቶሬ በበኩላቸው የክልሉን አመራር አቅም በመገንባት  መንግሥት ያስቀመጣቸውን  አቅጣጫዎች ለመተግበር ርብርብ መደረጉን አመላክተዋል።


 

ይህም በመንግሥት የሚነደፉ የልማት እቅዶች ወጥነት ባለው መልኩ ተፈፃሚ እንዲሆኑ አቅም መፍጠሩን አስረድዋል።

የርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመንግሥት  ተቋማት የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች አፈፃፀምን በመድረኩ ላይ አቅርበዋል።

በቀረበው ሪፖርት መሠረትም ''በትምህርት ለትውልድ'' እና ''አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ'' በሚል በተዘጋጀ የንቅናቄ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት በማሰባሰብ ለትምህርት ልማቱ መዋሉን በጠንካራነት አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም ከክልል፣ ከዞንና ከልዩ ወረዳ የተውጣጡ ከፍተኛ  አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም