ከተሞችን ዘመናዊ፣ ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ለተጀመሩ ስራዎች ውጤታማነት አመራሩ ህዝብን በማሳተፍ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- ከተሞችን ዘመናዊ፣ ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ለተጀመሩ ስራዎች ውጤታማነት በየደረጃው ያለ አመራር ህዝብን በማሳተፍ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ አስገነዘቡ፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የፅዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ንቅናቄ በይፋ አስጀምሯል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት፤ የጽዳትና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ከተሞችን ከማስዋብ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜዎች አሏቸው፡፡

ለአብነትም የስራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የፈጠራ ስራዎችን ማሳደግ፣ የአምራችነት አቅምን ለማጎልበት እና ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የጽዳትና የአረንጓዴ ልማት ስራ አሁን ላይ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመስፋት እየተተገበረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፣ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላትና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከተሞችን በዘላቂነት ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ ህብረተሰቡን የስራው ባለቤት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ከዚህ አኳያ የመንግስት ተቋማትም የዘወትር ስራቸው አካል ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡


 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የጽዳትና ውበት ንቅናቄው አሁን ላይ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለማስፋት ይሰራል ብለዋል፡፡

ከተሞችን ዘመናዊ፣ ውብ እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ዜጎችን ተሳታፊ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው እና የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሻፊ አህመድ በበኩላቸው በንቅናቄው የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት ህዝብን ንቁ ተሳታፊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በየአከባቢው ያሉ የመንግስት ተቋማትና አመራሩ በአርአያነት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያመላከቱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም