ከ10 ሀገራት የመጡ 18 ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ አየር ሃይልንና ዋር ኮሌጅን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- ከ10 ሀገራት የመጡ 18 ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ አየር ሃይልንና ዋር ኮሌጅን ጎብኝተዋል፡፡

ጎብኝዎቹ እንግሊዝ ውስጥ ከሚገኘው ከታዋቂው ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ዲፌንስ የመጡ ሲሆን የግሎባል ስትራቴጂ ፕሮግራም ኮርስ/GSPC/ ተማሪዎች መሆናቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከ10 ሀገራት የመጡ 18 ከፍተኛ ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች ሶስት የተቋሙን ዋና ዋና ክፍሎችን መጎብኘታቸውም ተጠቅሷል፡፡

በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የመከላከያ ትምህርት እና ስልጠና ዋና መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እና የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ለጎብኝዎቹ ሠፊ ገለፃ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

የመከላከያ ዋር ኮሌጅን ሲጎበኙ አሁናዊው የአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ምን እንደሚመስል በኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ ገለፃ እንደተደረገላቸውም እንዲሁ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ከጎበኙ በኋላ አጠቃላይ የአየር ሃይል እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል እና አየር ሃይሉ ለተቋሙ እያበረከተ ያለው ከፍተኛ ወታደራዊ አስተዋፅኦ ምን ያህል እንደሆነ በአየር ሃይል ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል በኩል ማብራሪያ ተሠጥቷል።

ጎብኝዎቹ ተቋሙን ለማወቅ እና ለመጎብኘት ላቀረቡት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ ግልፅ ባልሆኑላቸው ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ እና በጉብኝቱ ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎችም ተገቢ ምላሽ በማግኘታቸው መደሰታቸውን መናገራቸውም ተመላክቷል፡፡

ወደፊትም ከ10 ሀገራት ከመጡት መኮንኖች ጋር ሆነ እንግሊዝ ውስጥ ከሚገኘው ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ዲፌንስ ጋር የሚኖረው ትብብር እና ግንኙነት ጠንካራ ሊሆን እንደሚገባ በማንኛውም ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑ ሃሳብ ተነስቶ ውይይት መደረጉም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም