በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማት ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የማጎልበት ተግባር በትኩረት እየተከናወነ ነው

ሐረር፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፦ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማት በቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የማጎልበት ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

ደህንነቱ የተረጋገጠ ከተማን ለመፍጠር የሚያስችል (የሴፍ ሲቲ) የፕሮጀክት ግንባታ የውል ስምምነት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን  ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተፈራርሟል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በእለቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማት በቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የማጎልበት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የሐረር ከ1ሺ ዓመት በላይ እድሜ ያላት ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ መሆኗን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በተባበሩ መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ተቋም (ዩኔስኮ) ሁለት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ያስመዘገበች ከተማ መሆኗንም አክለዋል።

በመሆኑም የክልሉን የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።   

በተለይ በክልሉ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አንፃር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም በክልሉ የሚያከናውነው የፕሮጀክት ስራም ለዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታን እንደሚያበረክት ገልፀዋል።

በተለይ የጎብኚዎችን ደህንነት ከመጠበቅ፣ ወንጀሎችን አስቀድሞ ከመከላከል፣ የትራፊክ ፍሰትን ከመቆጣጠር፣ የከተማ ጽዳትና ውበትን ከመጠበቅና ከሌሎች ተግባራት አኳያ የፕሮጀክት ግንባታው ጠቀሜታ የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።

በከተማው የሚከናወነውን ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ የማጠናቀቅ ስራ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ሴልስ ቺፍ ኦፊሰር አቶ መሀመድ ሃጂ እንደገለፁት፤ የሴፍ ሲቲ ፕሮጀክት ግንባታ ደህንነቱ የተጠበቀ ከተማን ለመፍጠርና  የተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ የሚያግዝ ነው።

የፕሮጀክቱ ግንባታው በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው የዜጎችን ብሎም የጎብኚዎችን ደህንነት እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ ፕሮጀክቱ አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

የሴፍ ሲቲ የፕሮጀክት ግንባታ የውል ስምምነትን  የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘካርያ እና የኢትዮ ቴሌኮም ሴልስ ቺፍ ኦፊሰር አቶ መሀመድ ሃጂ ተፈራርመዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም