የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በተጀመረው ንቅናቄ የሚዲያና ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በተጀመረው ንቅናቄ የሚዲያና ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጠየቀ።

በአዲስ አበባ ከሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ”ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ የንቅናቄ መርሃ-ግብር መጀመሩ ይታወሳል።

የመርሃ-ግብሩ መሳካት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች አስተዋጽኦ በሚያደርጉበት ጉዳይ ላይ ባለሥልጣኑ ውይይት አድርጓል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ፤ የአካባቢ ብክለት በሰዎች ጤና እና አኗኗር ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የሚዲያና ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአካባቢ ብክለትን መከላከል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ አጠቃላይ ነዋሪው፣ ግለሰቦችና ተቋማት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የሚዲያና ኪነ-ጥበብ ሰዎች የግንዛቤ መፍጠርና የጉዳቱን ልክ በማሳየት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁነኛ አጋዥ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።


 

በባለሥልጣኑ የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ለሜሳ ጉደታ፤ የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በተቋሙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በ13 ሺህ ተቋማት ላይ ቁጥጥር ተደርጎ 2 ሺህ የሚሆኑት የብክለት መንስኤ በመሆናቸው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ጥረቶች መኖራቸውንም አንስተዋል።


 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አርቲስት ሙሉነህ ዘለቀ እና አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ በንፁህ አካባቢ መኖርና ከብክለት ነፃ የሆነ ከተማ መፍጠር የጋራ ጥቅማችን በመሆኑ በሚቻለው ሁሉ ንቅናቄውን ለማገዝ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም