በወለጋና አካባቢው ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላችንን እንወጣለን -- የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች

ነቀምቴ ፤ሚያዝያ 30/2016 (ኢዜአ)- በወለጋና  አካባቢው ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉ  ኢዜአ ያነጋገራቸው በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችና ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በተገኙበት ነቀምቴ ከተማ የለውጡን መንግስት ለመደገፍ ያለመ ሰልፍ ተካሄዷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከምስራቅ ወለጋ፣ ከምዕራብ ወለጋ፣ ከቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተውጣጡ ነዋሪዎች ከለውጡ መንግስት ጎን መሆናቸውን በተለያዩ መፈክሮች አረጋግጠዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሞሲሳ ፈይሳ፣ በወለጋና አካባቢው ያለው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ከለውጡ መንግስት ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ስልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋፍ ሰልፉ ላይ መገኘታቸውም ተስፋ እንደሰጣቸውና የተገኘውን ሰላም በማጽናት ለልማቱ መነሳሳት የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወለጋ ህዝብ ልማት እና ሰላም ፈላጊ መሆኑን በመረዳት በአካባቢው የተሻለ ልማት እንዲሚሰራ በመጥቀሳቸውም መደሰታቸውን የገለጹት አቶ ሞሲሳ፤የአካባቢው ልማት እንዲፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ሌላው ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለመገኘት መምጣታቸውን ያነሱት ሃደ ሲንቄ ደጊቱ ተስፋ  ዛሬ ከመቼውም በላይ ደስተኛ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

የወለጋ ህዝብ አቃፊና ሁሉን ወዳጅ መሆኑን የሚናገሩት ሃደ ሲቄ ደጊቱ፤ "መሬቱም ምርታማ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ወደ ልማት መዞር ይገባናል" ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች የተገኘው ሰላምና ልማት በወለጋ አካባቢም ዘላቂ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ወጣቶችም ከፀጥታ አካል ጋር በመሆን የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ "ወላጆችም ልጆቻችንን መምከር አለብን" ብለዋል።  

''የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝትና ያደረጉት ንግግርም በሰላም ተረጋግተን እንደምንኖር ተስፋ የሚሰጠን ነው'' ሲሉም ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወለጋና አካባቢው እየታዩ ያሉ ለውጦች ለፀጥታው መስፈን ማሳያ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ከዲጃ አብዱልቃድር ናቸው።

በቀጣይም የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና ልማትን ለማፋጠን ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ሰልፉ ላይ የተገኙት አቶ ናስር ሐሺን በበኩላቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋፍ ሰልፉ ላይ መገኘት ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም ከአካባቢያቸው ህዝብ ጋር በመተባበር ዘላቂ ሰላም እንዲኖርና ልማት እንዲፋጠን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አንስተዋል።

ሰልፉ ላይ ''ለውጡን እናጸናለን''፣ ''በሰላምም፣ በልማትም ምሳሌ ሆነን እናኮራዎታለን''፣ ''ሁሉንም አይነት ጽንፈኝነት እናወግዛለን'' የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተደምጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም