የኢትዮጵያንና የአሜሪካን የ120 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጉዞ የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቢሽን ተከፈተ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያንና የአሜሪካን የ120 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጉዞ የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቢሽን በብሔራዊ ሙዚየም ተከፍቷል።

"የ120 አመታት የሁለትዮሽ ግንኙነት ምስላዊ ጉዞ" በሚል መሪ ሃሳብ  በተከፈተው በዚሁ የፎቶ ኤግዚብሽን፤  በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር አርቪን ጆሴ ማሲንጋ፤ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች  ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር አርቪን ጆሴ ማሲንጋ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያና አሜሪካ 120 ዓመታትን የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በዛሬ እለት ለእይታ የበቃው የፎቶ ኤግዚቢሽን በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘርፈ ብዙ ወዳጅነት መኖሩንና  የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት  በየጊዜው እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል በጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ዘላቂ ልማትና በሌሎች የትብብር መስኮች ያለውን ጠንካራ ትስስር የሚያመላክት መሆኑንም እንዲሁ፡፡


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ ዘርፍ ጠንካራ መሰረት ያለው ወዳጅነት መኖሩን ጠቅሰው፤ ግንኙነቱ በባህልና ህዝብ ለህዝብ ትስስር ጭምር እያደገ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው እለትም ለእይታ የበቃው ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያና በአሜሪካን መካከል ለረዥም ዓመታት የዘለቀውን  ወዳጅነት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በብሔራዊ ሙዚየም የተከፈተው የፎቶ ኤግዚቢሸን እስከ ግንቦት 18 ቀን 20 16 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ ኤግዚቢሽኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ተቋም ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም