የፓስፖርት፣ ዲጂታል መታወቂያና የኤ ቲ ኤም ካርድ ማምረቻ ፋብሪካው መገንባት ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለምታደርገው ጉዞ አቅም የሚፈጥር  ነው - አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- የፓስፖርት፣ ዲጂታል መታወቂያና የኤ ቲ ኤም ካርድ ማምረቻ ፋብሪካ መገንባት ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለምታደርገው ጉዞ አቅም የሚፈጥር  መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፓስፖርት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የኤ ቲ ኤም ካርድና መሰል የደኅንነት ሕትመቶች ማምረቻ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃያት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱራህማን ኢድ ተገኝተዋል።



 
በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እና የቶፓን ግራቪቲ ኩባንያ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 
 
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፋብሪካው መገንባት ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለምታደርገው ጉዞ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
 
በእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር በኩልም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
 
የፋብሪካው መገንባት የሕትመት ዘርፉን ከማሳደግ እና ከማዘመን በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካ በዘርፉ መሪ ለመሆን በር ከፋች መሆኑንም ተናግረዋል።
 
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው፤ ቶፓን ግራቪቲ 120 ዓመት ያስቆጠረ አንጋፋ የሕትመት ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል።



 
በ137 ሀገራትም በምስጢራዊ ሕትመት ዘርፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ዛሬ መሠረቱ የተቀመጠው በአፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ኢትዮጵያና ጃፓን በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም