በድሬዳዋ የደም ልገሳው መርሃ ግብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ ቀረበ

ድሬዳዋ ፤ሚያዝያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በበጎ ፍቃደኝነት  ደም መለገስ  የሰውን ህይወት መታደግ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

በድሬደዋ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀንን ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተካሄዷል።

ደም የለገሱት የማህበሩ በጎ ፍቃደኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውም ታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ በሐር አደም በአደጋዎችና የተለያዩ ችግሮች ሳብያ የደም ፈላጊ ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን አንስተው የእነዚህን ወገኖች ህይወት ለመታደግ በበጎ ፍቃደኝነት የሚደረገው የደም ልገሳ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

ቀኑን አስመልክቶ ደም የለገሰው ወጣት አና አህመድ እንደተናገረው፤ ደም በመለገስ የሰው ህይወት ማዳን የመሰለ የህሊና ደስታ የሚሰጥ ነገር የለም ብሏል።

እኔ በለገስኩት ደም አንዲት ወላድ እናት ህይወቷን መታደግ መቻል የሚሰጠው መንፈሳዊ ደስታ ታላቅ በመሆኑ ሁሉም በዚህ ተግባር መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

ቀኑን ምክንያት በማድረግና በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር ከተማዋን የማፅዳት፣ ችግኝ የመትከል እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመመገብ ተግባራትም ተከናውነዋል።

እነዚሁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እስከሚቀጥለው እሁድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ታውቋል።

በእለቱ በተካሄደው የደም ልገሳ መርሃ ግብር 50 ዩኒት ደም መሰብሰቡ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም