በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡-በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ መፈቀዱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ኢንቨስትመንቱን ሊደግፉ የሚችሉ አስቻይ የሆኑ በርካታ የሕግ ማዕቀፍ ሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች ምርታቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ እንጂ ለሀገር ውስጥ ማቅረብ ሳይፈቀድላቸው መቆየቱን አብራርተዋል።

ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተጽዕኖ ሥር የነበሩ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ በመመሪያ መፈቀዱን ገልፀዋል።

ይህ የእርምጃ ኩባንያዎች ምርታማነትን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን ለሸማቹ ማኅበረሰብም የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አዋጅ መውጣቱን አስታውሰው፤ አዋጁ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ዞን እንዲሸጋገሩ የሚያደርግና በማክሮ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ከመሬት ፈቃድና አመራር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት እንደሚቀርፍ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራም  የራሱ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

አዋጁ የኢንቨስትመንት ከባቢን የሚፈጥር፣ ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ የሀገር ገጽታን የሚያጎድፉ ድርጊቶችን የሚያስወግድ፣ የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርና መናበብን የሚያጎለብት እንደሆነ ተናግረዋል። 

በተለይም ከከተሞች መስፋፋት እና በሊዝ መሬት አቅርቦት ዙሪያም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም መፍታት የሚችል የፖሊሲ እርምጃ እንደሆነ ነው ያነሱት።

በሌላ በኩል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ በነበሩ ዘርፎች በችርቻሮም ሆነ በጅምላ ንግድ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው መመሪያ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

የገቢና ወጪ ንግዱ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጉ በአነስተኛ ባለሃብቶች ተይዞ እና ብዙኃኑ በሚማረርበት የአቅርቦት ገበያና የተጋነነ ዋጋን በማቃለል ረገድ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ አንስተዋል።

ለገበያው በሕግ የሚመራ ሥርዓት መበጀቱ ተወዳዳሪነትን፣ የምርት ጥራት የሚጨምር እና የሸማቹን ማኅበረሰብ ክፍል የሚደግፍ እንደሆነ ገልፀዋል። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም