በአማራ ክልል ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን ሊያጠናክር ይገባል-የክልሉ ጤና ቢሮ

ባህር ዳር፤ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)-በአማራ ክልል ህብረተሰቡ በፈቃደኝነት ደም የመለገስ ባህሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ጤና ቢሮ አስገነዘበ።

የቢሮው አመራር አባላትና ሠራተኞች ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የደም ልገሳ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ በሰጡት አስተያየት፤ “ደም የምንለግሰው በደም እጥረት ምክንያት ለሞት አደጋ የተጋለጡ እናቶች፣ ህፃናትና አዋቂዎችን ለመታደግ ነው" ብለዋል።


 

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች 80 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር ቢገባም ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 50 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በደም አቅርቦት እጥረት ምክንያት የቀዶ ህክምና አገልግሎት ቀጠሮ ያላቸው ግለሰቦች የህክምና አገልግሎት በወቅቱ ማግኘት እየቻሉ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም የተከሰተውን የደም እጥረት ችግር በመፍታት በሕክምና ተቋማት የተሟላ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ህብረተሰቡ በፈቃደኝነት ደም በመለገስ ህይወትን እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።

"ለራሱ ህይወት ዋጋ የሚሰጥ ሰው ለሌሎችም ደም በመለገስ ዋጋ ይሰጣል’’ ያሉት ደግሞ በቢሮው የልብና የደም ስር በሽታዎች ፕሮግራም ማናጀር ዶክተር ሞላ ሞገስ ናቸው።


 

ደም የሚለግስ ሰው ለህይወት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ደም በመለገስ በሞት አፋፍ የምትገኝን ነፍስ ከማትረፍ በላይ ለህሊና እርካታ የሚሰጥ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። 

ደም የሰውን ህይወት ለመታደግ ያለውን ጥቅም በመረዳት ለ30 ጊዜ ያህል ደም በመለገስ የወገን አለኝታነታቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውንም ዶክተር ሞላ ተናግረዋል።


 

በቢሮው የህክምናና ተሃድሶ ዳይሬክተር ዶክተር ማረው ጌጡ በበኩላቸው፤ የተለገሰው ደም ለሚፈሳቸው እናቶች፣ የደም እጥረት ላጋጠማቸው ህፃናትና በአደጋ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማትረፍ መሆኑን ገልጸዋል።

"በክልሉ በጤና ተቋማት ያለውን የደም እጥረት ለማቃለል እኛ የጤና ባለሙያዎችና የቢሮው ሠራተኞች ደም በመለገስ ህይወትን ለመታደግ እየሰራን ነው'' ብለዋል።

በደም አቅርቦት እጥረት ምክንያት የሰው ህይወት እንዳያልፍ ሁሉም ሰው ደም በመለገስ ህይወትን መታደግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት ከ93ሺህ በላይ ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም