በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በተደረገው ጥረት ውጤት ተመዝግቧል

አዳማ ፤ሚያዝያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በክልሉ ለኤች አይ ቪ ኤድስ  ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ቡሻ በለኮ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

''ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የደም ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ የህክምና ክትትል እንዲያገኙና የዘርፉን ህክምና ማሻሻል እንዲሁም መድኃኒት የጀመሩ ዜጎች በደማቸው ያለው የቫይረስ መጠን እንዲቀንስ ማስቻል ላይ እየሰራን እንገኛለን'' ብለዋል።

በተለይ በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በኮሌጆች፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች አካባቢዎች እንዲሁም በቡና ቤቶች አካባቢ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በሽታውን በመከላከሉ ረገድ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎን በማሳደግ ረገድ የተሻለ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።

ጉዳዩ አሁንም ትኩረትን የሚፈልግ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ቡሻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ምርመራ በማድረግ 8 ሺህ 76 በሚሆኑት ላይ ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱን ጠቁመዋል።

አዳዲስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርን በመቀነስ ረገድ አምና ከነበረው 0 ነጥብ 4 በመቶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 0 ነጥብ 3 በመቶ ማውረድ መቻሉን ገልፀዋል።

አሁንም በዋና ዋና መንገድ መተላለፊያ ላይ የሚገኙ ከተሞች የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋልባቸው በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝባቸው 132 ሺህ 685 ዜጎች ውስጥ መድኃኒት የጀመሩት 129 ሺህ 158 መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ዘርፉ ናቸው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘው ከ8 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ ከ7ሺህ በላይ የሚሆኑት የመድኃኒት አገልግሎት መጀመራቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአሰላ ከተማ ጤና ጽሕፈት ቤት የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ አስተባባሪ አቶ ቆርቾ ሃጂ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ናቸው።

በተለይ በማህበረሰቡ ውስጥ መዘናጋት እንዳይፈጠር የማንቃትና የማስተማር ስራ በፋብሪካዎች፣ በቡና ቤቶችና የቀን ሰራተኞችን ጨምሮ ረጅም ርቀት ተጓዥ በሆኑ አሽከርካሪዎች ላይ ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

 

 

 

    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም