የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መጠናከር አለበት

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠንና  የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የፖሊሲ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርሃተስፋ (ዶ/ር )ገለጹ።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂን እውን ለማድረግ በመንግስት የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ ''ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025'' ስትራቴጂ ወጥቶ እየተተገበረ ይገኛል።

ስትራቴጂው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና የ10 አመት መሪ የልማት እቅድ ስትራቴጂዎች  እንዲሁም ከአፍሪካ  የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጋር ተሳስሮ የሚተገበር ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የፖሊሲ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርሃተስፋ (ዶ/ር)ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ዓለም በፍጥነት እየሄደበት የሚገኝ ወሳኝ ጉዳይ ነው።

በሀገሪቷ ያሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና ቴክኖሎጂውን  ለማስረጽ ድርሻቸውን ወስደው መንግስትና የግሉን ዘርፍ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ዲጂታላይዜሽንን ለማስረጽ በቴሌኮም ዘርፉ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሚበረታታ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እስከ 5G  ኔትዎርክ መዘርጋቱ ለዚሁ አካሄድ አመቺ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በመጪው ጊዜያት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ስለሚኖራት ቴክኖሎጂውን እውን ለማድረግ ሰፊ እድል እንዳላት ተናግረዋል፡፡

በፋይናንስ ፖሊሲ እየታዩ ያሉ አበረታች ለውጦች ፣ የካፒታል ገበያ መቋቋሙ ፣የውጭ ኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች መጠናከር ወጣቶች በፈጠራ የታገዘ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

ስትራቴጂው በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ብቻ ሊተገበር ስለማይችል የዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፎ መጠናከር አለበት ነው ያሉት።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግስት፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጀንሲዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የሀገሪቷን የዲጂታል ጉዞ ከአህጉሪቱ ስትራቴጂ ጋር በማስተሳሰር ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በመታገዝ ስትራቴጂውን እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገች መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በፖሊሲ አቅጣጫ የሚተገበረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በመንግስት አሰራር ላይ ኢ-ገቨርንመንት አስተዳደርን ለመተግበር ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

ስትራቴጂው የኢ-ኮሜርስ ንግድን በዲጂታል ለማስኬድ፣ የምርምር ስራዎችንና አጠቃላይ የትምህርት ዘርፉን  በዲጂታል ለማሳለጥ የሚያስችል እንደሚሆን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም