ኢትዮጵያ የሱዳንን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት መደገፏን አጠናክራ ትቀጥላለች 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የሱዳንን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ እስካሁን የተጫወተችውን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የሱዳን ሪፐብሊክ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሁሴን አዋድ አሊ መሃመድን በዛሬው እለት ተቀብለው አነጋግረዋል። 

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና በሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ውይይት አድርገዋል። 

አምባሳደር ምስጋኑ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ የሱዳንን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ እስካሁን የተጫወተችውን ሚና አውስተው አበርክቶዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። 

አክለውም ኢትዮጵያ፣ የሱዳን ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት በሱዳናውያን ባለቤትነትና መሪነት መከናወን አለበት የሚል ፅኑ እምነት እንዳላትም ገልጸዋል። 

የሱዳን ሪፐብሊክ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አምባሳደር መሀመድ ሁሴን  በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሱዳን ሁለንተናዊ የሰላም ማስፈን ሂደት ውስጥ እየተጫወተችው ያለውን ሚና በማድነቅ በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እና ወንድማማቻዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተ ወሳኝ ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። 

አምባሳደር ሁሴን በቅርቡ የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ኢትዮጵያን የመጀመሪያ የጉብኝታቸው መዳረሻ ማድርጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም