የዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለውጭ ገበያ የሚላክ የአቮካዶ ዘይት ማምረት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለውጭ ገበያ የሚላክ የአቮካዶ ዘይት ማምረት ጀመረ
ዲላ ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- የዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለውጭ ገበያ የሚላክ የአቮካዶ ዘይት ማምረት መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
ፓርኮ በአንድ ፈረቃ በቀን 50 ሺህ ቶን አቮካዶ በመፍጨት 2ሺህ 500 ሊትር ዘይት እንደሚያመርትና በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ ለኢዜአ እንዳሉት በዲላና ይርጋጨፌ በሚገኙ ፓርኮች ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 15 ባለሃብቶች ወደስራ ለመግባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው።
በተለይ በአቮካዶ ዘይት፣ ቡና፣ ወተትና ማር ማቀነባበር የሚያስችል የማሽን ተከላን ጨምሮ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ከእነዚህ ውስጥም በ60 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደስራ የገባው "ሲይዚ አግሮ ኢንዱስትሪ" የተሰኘ ዘይት ፋብሪካ ለውጭ ገበያ የሚሆን የአቮካዶ ዘይት ምርት ማምረት መጀመሩን ገልጸዋል።
ፋብሪካው ከአቮካዶን ተረፈ ምርት ለእንስሳት የሚሆን መኖ እንደሚያዘጋጅም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
የፋብሪካው ሥራ መጀመር ለበርካቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ለገበያ ትስስር፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
በፓርኮቹ የሃይል አቅርቦት፣ የግብዓትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መሟላቱን የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች በቀረው ውስን ቦታ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ፋብሪካው በቀን በአንድ ፈረቃ ከ50 ሺህ ቶን በላይ አቮካዶ በመፍጨት ከ2 ሺህ 500 ሊትር በላይ ዘይት ማምረት መጀመሩን ያነሱት ደግሞ የሲይዝ አግሮ ኢንዱስትሪ ዘይት ፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋቲሶ ዋንጫ ናቸው።
ለፋብሪካው ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን ከሚያመርቱት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፋብሪካው ለ50 ሠራተኞች ከፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል በተጨማሪ በምርት አቅርቦት ትስስር በ17 ማህበራት የታቀፉ 15 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
ፋብሪካው የመጀመሪያ ምርቱን በቀጣይ ሰኔ ወር በአሜሪካን ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሃንጅንሶ የአትክልትና ፍራፍሬ ማህበር ሰብሳቢ አቶ እንዳለ አዱላ በበኩላቸው ማህበሩ 62 አቮካዶ አምራች አርሶ አደሮችን በማቀፍ በየወሩ 300 ኩንታል ምርት ለፋብሪካው እያቀረበ ነው።
በአሁኑ ወቅት እስከ 1ሺህ ኩንታል የማቅረብ አቅም እንዳላቸው የተናገሩት አቶ እንዳለ፣ በቀጣይ የምርት መቆራረጥ እንዳይፈጠር የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በስፋት ወደ ማልማት መግባታቸውን ገልጸዋል።
ፓርኩ በአካባቢያቸው በመከፈቱና ወደ ምርት መግባቱ የሥራ እድል ለማግኘት እንዳስቻለው የገለጹት ደግሞ ወጣት ትንሳኤ ኢያሱ እና ህብስት ዓባይነህ ናቸው።
በስራቸው ውጤታማ በመሆን ራሳቸውም ሆነ ፋብሪካውን ተጠቃሚ ለማድረግ ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርኩ ወደሥራ መግባቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በዘርፉ የእወቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር እድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ፓርኮቹ በ20 ሄክታር መሬት ላይ ያረፉ ሲሆን በውስጣቸው ከ30 በላይ ፋብሪካዎች የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ታውቋል።
በሙሉ አቅማቸው ወደሥራ ሲገቡም ከ100ሺህ በላይ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።