ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች እውን ሆነዋል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡-ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች እውን መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

በወለጋ ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን፤ በድጋፍ ሰልፉ ከአራቱም የወለጋ ዞኖች የተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ 

በድጋፍ ሰልፉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ስኬቶችን የሚገልጹ መልዕክቶችም ተላልፈዋል፡፡

ከተላለፉ መልዕክቶች መካከል ሰላማችንን በመጠበቅ ድላችንን እናጸናለን፤ በሰላምና በይቅርታ መንገድ ሁሉም አሸናፊ ነው፤ ከብልጽግና ጉዟችን የሚገታን ፈተና አይኖርም፤ እና የአሸባሪው ሸኔ ድብቅ ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብን ወደ ባርነት መመለስ ነው፤ የሚሉ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ለውጡን ለማጽናት ማንኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን፤ ወለጋ የሰላምና የብልጽግና ምድር፤ ድላችንን እንጠብቃለን ለቀጣይ ስኬት በጋራ እንሰራለን፤ እና መሪያችን ብልጽግናን በማሳካት ህልምህን እውን እናደርጋለን ፤የሚሉና ሌሎችም ይገኙበታል።   

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶር) መሪነት በርካታ የልማት ድሎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በስንዴ ልማት ፤ አረንጓዴ አሻራ፣በመሰረተ ልማት ተደራሽነትና በሌሎች የልማት ስራዎች ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማስቀጠል የተጀመሩ ስራዎች በሁሉም መስክ ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ነው ያነሱት፡፡  

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋሙ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች እውን መሆናቸውንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የልማት ኢንሼቲቮች በክልለ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ እያደረጉ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ 

የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ አንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት፣ ልማትን ለማደናቀፍ እና ሰላም እንዳይረጋገጠ ለማድረግ የሚሰሩ አካላትን ህዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሊታገላቸው እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

ወለጋ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን አብሮነት በማጠናከር ሁሉም ለሰላም መስፈንና ልማት መረጋገጥ በጋራ እንዲሰራም መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡ 

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ ምስጋኑ ቱሉ በበኩላቸው ባለፉት የለውጥ ዓመታት የነቀምቴና አካባቢው ማህበረሰብን በተጨባጭ ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም